2 Samuel 5

ዳዊት በእስራኤል ላይ ነገሠ

5፥1-3 ተጓ ምብ – 1ዜና 11፥1-3 1የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ 2ባለፈው ሳኦል በእኛ ላይ ነግሦ በነበረ ጊዜ፣ እስራኤልን በጦርነት የምትመራቸው አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”

3ስለዚህም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም ኬብሮን ላይ በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።

4ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ አርባ ዓመትም ገዛ። 5በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር፣ ኢየሩሳሌም ሆኖም በመላው እስራኤልና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።

ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል አደረገ

5፥6-10 ተጓ ምብ – 1ዜና 11፥4-9 5፥11-16 ተጓ ምብ – 1ዜና 3፥5-9፤ 14፥1-7 6ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ሄዱ። ኢያቡሳውያንም፣ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፣ “ዕውሮችና ዐንካሶች እንኳ ይከለክሉሃልና ወደዚህች አትገባም” አሉት። 7ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ዐምባ ያዘ፤ ይህችም የዳዊት ከተማ የተባለችው ናት።

8በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶች
ወይም ማንጠልጠያ ኵላቦች
ወደሚሆኑ፣ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው
ወይም በዳዊት የተጠላ
ሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው።

9ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት። 10የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ።

11በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ ዐናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን አብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት። 12እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን እንዳሰፋለት ዳዊት ዐወቀ።

13ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ ከበፊቶቹ በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ሌሎች ቁባቶች አስቀመጠ፤ ሚስቶችም አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት። 14በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ 15ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ናፍያ፣ 16ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ።

ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ

5፥17-25 ተጓ ምብ – 1ዜና 14፥8-17 17ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ለመፈለግ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ግን ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ። 18በዚህ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። 19ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ፍልስጥኤማውያንን ወጥቼ ልውጋቸው? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጠኛለህ?” ሲል ጠየቀ።

እግዚአብሔርም፣ “አዎን ሂድ፤ በርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።

20ስለዚህም ዳዊት ወደ በአልፐራሲም
በአልፐራሲም ማለት የሰባበረ ጌታ ማለት ነው።
ሄዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው። እርሱም “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ፣ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” አለ። ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም በአልፐራሲም ተባለ።
21ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሽተው ስለ ነበር፣ ዳዊትና ሰዎቹ ወስደው አቃጠሏቸው።

22ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። 23ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በስተ ኋላቸው በኩል በመክበብ በበለሳኑ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤ 24በበለሳኑ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጕዞ ድምፅ ስትሰማም፣ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት ቀድሞህ ወጥቷል ማለት ነውና በዚያን ጊዜ በፍጥነት ወደ ፊት ሂድ።” 25ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ከገባዖን
የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል (1ዜና 14፥16 ይመ)፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ጊባ ይላል።
እስከ ጌዝር ድረስ እያሳደደ መታቸው።

Copyright information for AmhNASV